• News

 • News

 • ‹‹አዲስ አበባ የሁላችን ናት›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) Posted on 29 March 2019

  ‹‹አዲስ አበባ የሁላችን ናት›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አዲስ አበባ ‹‹የእኛ ናት›› የሚል ክርክር በስፋት እንደሚነሳ በማውሳት ለተጠየቁት ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ‹‹አዲስ አበባ የሁላችን ናት፤›› በማለት የመለሱ ሲሆን፣ ‹‹በመሠረቱ አዲስ አበባ የማን ናት የሚል ጥያቄ በእኛ ደረጃ አንስቶ መወያየት አሳፋሪ ነው፤›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

  ‹‹አዲስ አበባ የማን ናት፣ የማን አይደለችም እያሉ የሚከራከሩ ሰዎች ከጭንቅላታቸው ጀርባ ምን አስቀምጠው ነው የሚነጋገሩት የሚለውን በራሳቸው አውድ መመልከት ያስፈልጋል፤ ምን ታስቦ ነው የማናት የሚባለው?›› በማለት፣ ‹‹አዲስ አበባ የእኔ ናት ስል የአንተ አይደለችም ማለት ከሆነ ስቼያለሁ፡፡ የእኔ ሆና የአንተ እንዳሆነች የምናገር ከሆነ ስህተት ነው፡፡ አዲስ አበባ የሁላችንም ናት፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

  በታሪክ የፌዴራል ሥርዓቱ ሲዋቀር አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል አካል የማድረግ ፍላጎት እንደነበረ ገልጸው፣ ነገር ግን ባጠራት ክልል ውስጥ ባላት ግንኙነት የተነሳ ክልሉ ልዩ ጥቅም ማግኘት አለበት የሚል በሕገ መንግሥቱ ተቀምጧል በማለት ያብራሩ ሲሆን፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሁን ባለበት አቅጣጫ በትክክለኛ መንገድ እንዳይሄድ ባልባሌ ጉዳይ ጊዜ እንድናባክን የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው ይህንን ሐሳብ የሚያንሸራሽሩት፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ለአዲስ አበባ ሰዎች ይኼ አጀንዳ ሊሆን አይችልም፡፡››

  ‹‹አዲስ አበባ የእኛ ናት ስንል መነሻችን ምንድነው?›› በማለት የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የዛሬ 20 ዓመት በአዲስ አበባ የአሁኑን ያክል ሰው እንዳልነበረ፣ ብሎም ባለፉት 20 ዓመታት ይኼንን ያክል ሰው በአዲስ አበባ እንዳልተወለደ በመጥቀስ፣ አዲስ አበባ ከፍቶትም ሆነ ተደስቶ የመጣውን ኢትዮጵያዊና የውጭ አገር ዜጎች አቅፋና ተሸክማ ኖራለች ብለዋል፡፡ ነገር ግን ‹‹በሚያሳዝን ሁኔታ በኩራዝ የሚኖሩ ዜጎች ያሉባት ከተማ ስለሆነች ይህችን ከተማ እንዴት እንቀይራት ነው የእኛ ጉዳይ መሆን ያለበት፤›› ሲሉም አስምረዋል፡፡

  ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ያላት ልዩ ጥቅም ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ፣ እንዴት ይተግበር የሚለው ላይ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል አስተዳደሮች በጋራ መምከር አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል፡፡

  በተያያዘም ለአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ማስዋብ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አዘጋጅነት በሰሀን አምስት ሚሊዮን ብር የሚሸጠው እራት በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ እንደሚካሄድ በማመላከት፣ ለእራት የሚታደሙ ሰዎች እንደ ስጦታ ሳይሆን በረዥም ጊዜ ውጤቱ የሚታይ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ እንደሆነ በመረዳት ሁሉም እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

  በዚህ ፕሮጀክት ለመሳተፍና ለመደገፍ ኬንያ፣ ግብፅ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲና ሌሎች አገሮች ፍላጎት እንዳሳዩ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቻይና የፕሮጀክቱን መነሻ በሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት ላለው 12.5 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ማልሚያ የዲዛይንና የትግበራ እገዛ ማድረጓን አስታውቀቃል፡፡ ይህ ስፍራ በአንድ ጊዜ ከ100 ሺሕ በላይ ሰዎችን መያዝ የሚችል ስፍራ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አካልና በአንድ ጊዜ 20 ሺሕ ሰዎችን መያዝ የሚችል ቤተ መጻሕፍት እንደሚገነባም ጠቁመዋል

  « Back to news archive