• News

 • News

 • የአገራዊ ደኅንነት ሥጋት የሆነው የብሔር ፖለቲካ Posted on 15 April 2019

  የአገራዊ ደኅንነት ሥጋት የሆነው የብሔር ፖለቲካ

  በመጋቢት 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ የነበረው ከልክ ያለፈ ደስታና ፌሽታ ቀስ በቀስ እየረገበ የመጣ ይመስላል፡፡ እርሳቸው ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት አገሪቱን ሲንጣት የነበረው ግጭት፣ ሁከት፣ ብጥብጥና አመፅ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በተወሰነ ደረጃ የቀነሰ ቢመስልም፣ ግጭቶች ተመልሰው ሲያገረሹና በየቦታው አዳዲስ ግጭቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡

  እነዚህ አዳዲስ ግጭቶች ከኢኮኖሚያዊና ከሰብዓዊ ቀውሶች ጋር ተዳምረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን አስተዳዳር መፈተን የጀመሩም ይመስላል፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ በቅርቡ በአጣዬና በኦሮሞ ልዩ ዞኖች የተቀሰቀሰውን ግጭት ማንሳት የሚቻል ሲሆን፣ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በአጥፊዎች ላይ ተመጣጣኝ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር፡፡ ይህ ተመሳሳይ ክስተትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር በዕለት ተዕለት ግጭቶችን ለመፍታት የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ሠራዊት አባላትን ማሰማራት ላይ እንዲጠመድ ምክንያት ሆኖታል፡፡

  በጥር 2011 ዓ.ም. የወጣው የአሜሪካ የደኅንነት ማኅበረሰብ የዓለም ሥጋቶች ዳሰሳ ሪፖርት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በውስጥ ጉዳዮቻቸው እንደሚፈተኑ ይተነብያል፡፡

  ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ከባድ ውስጣዊ ውጥረቶችን ያስተናግዳሉ፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ የፖለቲካ ቁጥጥርን ከለውጥ ፍላጎቶች ጋር ለማጣጣም ይታገላሉም፤›› ሲልም ሪፖርቱ ምልከታውን አስቀምጧል፡፡

  ምንም እንኳን የእነዚህ ግጭቶችና ብጥብጦች መነሻ ከቦታ ቦታና ከአተያይ ሊለያይ ቢችልም፣ የብሔር ፖለቲካ ያለው አስተዋጽኦ ግን ማዕከላዊ ሥፍራ እንደሚይዝ በርካቶችን ያስማማል፣ መንግሥትን ጨምሮ፡፡

  መጋቢት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. የአገሪቱን የደኅንነት ተቋማት ሪፎርምን በሚመለከት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅነነት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የብሔራዊ ፖለቲካ የአገራዊ ደኅነነት የሥጋት ምንጭ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጥፋተኞች ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሲሉ በብሔራቸው ውስጥ እንደሚደበቁ፣ የግለሰብ ጠብ እንኳን የብሔር ግጭት መልክ እንደሚይዝ ያወሱት አማካሪ ሚኒስትሩ፣ ለብሔር የተሰጠውን ቦታ ከአገራዊ ማንነት ጋር ማመጣጠን ባለመቻሉ የተከሰተ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

  ‹‹የአገራዊ ደኅንነታችን ሥጋት አክራሪ ብሔርተኝነት ነው፤›› በማለት ሪፖርተር ላነሳላቸው የማብራሪያ ጥያቄ መልስ የሰጡት አቶ ተመስገን፣ ‹‹ይኼኛው የብሔር ፖለቲካ ዋናው ነው እንጂ ብቸኛው አይደለም፡፡ ሁሉም ድርጊቶች አገራዊ ማንነትን የረሱ ናቸው፡፡ በአንድ ብሔር ውስጥ እንኳን ያሉ ክፍፍሎች በርካታ ናቸው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

  ነገር ግን ይኼ የብሔር ፖለቲካ እንዴት የአገራዊ ደኅነነት ሥጋት ሊሆን ይችላል የሚለው አከራካሪ ሊሆን እንደሚችል የሚያምኑት አቶ ተመስገን፣ ዕለት ተዕለት ከሚያዩዋቸው ጉዳዮች በመነሳት የተደረሰበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

  የፌዴራል ሥርዓቱና የአገሪቱ የፖለቲካ አሠራር በብሔር ፖለቲካ ላይ በመመሥረቱ፣ የአቶ ጥሩነህን መግለጫ የተከታተሉ በርካታ ግለሰቦች መሠረታዊው የአገሪቱ የፖለቲካ መዋቅርና የፌዴራል ሥርዓቱ ላይ አዲስ ለውጥ ይመጣል ሲሉ ያስባሉ፡፡ በተጨማሪም ኢሕአዴግ በብሔር ላይ የተመሠረተውን ማንነቱን ሊተው ይችላል የሚሉ መላ ምቶችም ተስተውለዋል፡፡ ነገር ግን አቶ ጥሩነህ የሥጋቱ ልየታ ይኼንን አያመላክትም ባይ ናቸው፡፡

  ‹‹ይኼ ማለት የፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀር ይቀየራል ማለት አይደለም፣ እርሱ ሰፊ ውይይት የሚጠይቅ ነው፡፡ በማንነት ላይ የተመሠረተ መፈቃቀድ ያመጣው ሥርዓትና የራስን ማንነት ማክበር ሁሌም ይቀጥላሉ፡፡ ነገር ግን አስተሳሳሪ የሆነው ኢትዮጵያዊ ማንነት ነው፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

  እስካሁን ከአገራዊ ማንነት በተቃራኒው ሲሠራ መቆየቱን የተናገሩት አቶ ተመስገን፣ ለብሔር የተሰጠው ግምት ትልቅ በመሆኑ ከአገራዊ ማንነት ጋር የማመዛዘን ሥራ መሠራት አለበት ይላሉ፡፡

  በአገራዊና በብሔራዊ ማንነነት መካከል የሚመዛዘን ሥራ መሠራት እንዳለበት የሚያምኑት የፖለቲካና የደኅንነት ባለሙያው አቶ አበበ አይነቴ፣ አማካሪ ሚኒስትሩ ለዚህ መደምደሚያ መነሻ ያደረጉት ምን እንደሆነ ማወቅ ባይቻልም፣ የአገሪቱ ችግር የብሔር ፖለቲካዊ በራሱ ሳይሆን በአግባቡ መተግበርና ማስተዳደር ያልተቻለ የብሔር ፖለቲካ ነው ይላሉ፡፡

  የሕግ የበላይነት መኖር፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ የደኅነነት ተቋማት ያላቸው የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ አቅምና መንግሥት ያለበትን የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት በምን ደረጃ እየተወጣ ነው የሚሉት መጤን ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው የሚሉት አቶ አበበ፣ በእርግጥ በብሔርና በአገራዊ ማንነቶች መካከል የሚመጣጠን ሥራ ማከናወን ይገባል ይላሉ፡፡

  ኢሕአዴግ ከ28 ዓመታት በፊት ወደ ሥልጣን ሲመጣ የብሔር ጭቆና አለ ብሎ ቢመጣም በቅጡ መፍጥሔ አልሰጠም ያሉት አቶ አበበ፣ ካለፈው ስህተት ለመማር አለመቻልና ቀዳሚውን ጥያቄ መመለስ ባለመቻሉ አሁን ያለው ሁኔታ ሊከሰት ችሏል ይላሉ፡፡ ይኼንንም ሕገ መንግሥቱን በመተግበር ሊፈታ ይችል እንደነበር በመጠቆም፣ ተቃዋሚዎች አይተገበርም ቢሉም መንግሥት እየተገበርኩ ነው ሲል ክርክር መግጠሙ ጊዜ አባክኗል ይላሉ፡፡

  ሕገ መንግሥቱ በብሔር ማንነትና በብሔር ብሔረሰቦች ምሰሶነት የቆመ ነው በማለት ያብራሩት አቶ አበበ፣ ብሔር ብሔረሰቦችን በሥጋት ማየት አይቻልም ይላሉ፡፡

  ‹‹የዴሞክራሲ ባህላችን በአሸናፊና በተሸናፊ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ልዩነቶቻችንን ያለመቀበል ችግር አለ፡፡ ዴሞክራሲ የሚያስፈልገው ደግሞ የጨፍላቂነት፣ የበላይነትና የበታችነትን ሚዛን ለመጠበቅ ነው፤›› የሚሉት አቶ አበበ፣ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ዕርቅ ፈላጊነት ላይ ያተኮሩ ናቸው እንጂ አሸናፊና ተሸናፊን ለመለየት አይደለም ይላሉ፡፡ ትኩረታችን የምንፈልገው መፃኢ ሁኔታን ማሻሻል ነው፡፡

  ‹‹አሁን ያለፈውን የማወራረድ ትርዒት አለ፡፡ ሌላው አጥፊ ነው፣ የእኔ ብቻ ነው ትክክል የሚል አስተሳሰብ ከባህላችን ያፈነገጠ ነው፤›› ሲሉም ይወቅሳሉ፡፡

  የቡራዩ ግጭትን ተከትሎ በአርባ ምንጭ ለተቃውሞ በንዴት የወጡ ወጣቶችን እርጥብ ሳር ይዘው በመንበርከክ ከጥፋት ያስቆሟቸው አባቶች በሌላ ቦታ ተሞክሮ ያልተቻለ ስኬት እንዴት አስመዘገቡ በማለት የሚጠይቁት አቶ አበበ፣ የጋሞዎቻ የችግር አፈታት ሥልት ከነባሩ ባህላዊ እሴት የተቀዳ በመሆኑ እንደተሳካ ይናገራሉ፡፡ ስለዚህም ግጭቱን በቀላሉ ማብረድ ችለዋል በማለት ይኼንን ወደ ዘመናዊ ዴሞክራሲ በማምጣት፣ ለችግሮችና ወደ አረመኔነት ለተሸጋገረው የብሔር ፖለቲካ ችግር መፍትሔ ማግኘት ይቻላል ይላሉ፡፡

  ትናንትም ዛሬም መሻገር ያልተቻሉ የኢትዮጵያ የሥጋት ምንጭ ውስጣዊ ሁኔታዎች ናቸው የሚሉት አቶ አበበ፣ ‹‹ይኼንን ከተወጣን የውጭውን ድል ማድረግ እንችላለን፣ ሁልጊዜም ውስጣችን ሲዳከም ነው ጠላት የሚመጣብን፤›› ሲሉም ያሳስባሉ፡፡

  ‹‹የውጭ ተጋላጭነታችንን የሚጨምረው የውስጥ ችግራችን ነው፡፡ ይኼንን ከፈታን ለውጭዎች ሁሉ አለኝታ መሆን እንችላለን፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡

  ነገር ግን የሚደረጉ ለውጦች ሁሉ ባለው ላይ መጨመር እንጂ ከባዶ መጀመር የለባቸውም በማለት ያስጠነቅቃሉ፡፡

  ታዋቂው ምሁርና የፖለቲካ ፓርቲ አመራር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) የብሔር ፖለቲካ የዛሬ 50 ዓመት ገደማ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደገባ በማስታወስ፣ የብሔር ማንነትና አገራዊ ማንነትን ማመጣጠን አልተቻለም የሚለው ግምገማ ኢሕአዴግን እንደሚመለከት በመግለጽ፣ ተጠያቂነትን ለመሸሽ በብሔራቸው ውስጥ የሚደበቁ መኖራቸው ግን አይካድም ይላሉ፡፡

  ከብሔር ፖለቲካ ጋር የተያያዙ ችግሮች ቢኖሩም፣ በአግባቡ ባለመፈታታቸው ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ከአገሪቱ ጋር አብረው ዘልቀዋል ይላሉ፡፡

  ‹‹የብሔር ጭቆና አለ ብሎ ተነስቶ እፈታለሁ በማለት የመጣው ኢሕአዴግም ጨቋኝ ሆኖ ቀጠለ፤›› የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ ‹‹ኢሕአዴግ የብሔር ፖለቲካ ችግርና ሥጋት መሆኑ የዛሬ ጉዳይ አይደለም፤›› ይላሉ፡፡ እንደ እርሳቸው ምልከታ የኤርትራን መገንጠል ያስከተለውም ይኼው የብሔር ፖለቲካ ችግር ነው፡፡

  የሕዝቡን አንድነት በማጠናከር በጋራ ለመኖር ለዚህ ያህል ጊዜ አብሮን የኖረን የብሔር ፖለቲካ ችግር መፍታት አለብን የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ ሁሉንም በእኩል ባሳተፈና ለብዙኃኑ ተቀባይነት ባለው መልኩ መፈታት አለበት ይላሉ፡፡

  እስካሁን በብሔር ፖለቲካው ለመጣው ችግር ሁሉ ተጠያቂው፣ ብሎም በቀጣይ መፍትሔ አፍላቂው የተማረው ማኅበረሰብ ነው ብለው የሚወቅሱና የሚያሳስቡ ሲሆን፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ጽንፍ ያሉት ወደ መሀል የሚመጡበት አመራር እንዲቀመጥ ያሳስባሉ፡፡

  የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲ በመሻሻል ላይ ያለ ሲሆን፣ የብሔር ፖለቲካ ሥጋት እንዴት ወደ ፖሊስ ሰነድነት ሊቀየር እንደሚችል ግልጽ አልሆነም፡፡ እንደ አቶ ተመስገን ገለጻ፣ የብሔራዊ ደኅንነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች ለየብቻ መሠራት እንዳለባቸው ታምኖ እየተዘጋጀ ሲሆን፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለሕዝብ ውይይት ይፋ ይሆናል፡፡

  ነገር ግን የብሔር ፖለቲካው እንደ ሥጋት ተወስዶ ወደ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሲቀየር ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ አቶ አበበ ያስረዳሉ፡፡

  ‹‹የብሔር ፖለቲካ በራሱ የደኅንነት ችግር ነው ብሎ ከተነሳ ችግር ነው የሚሆነው፣ ሚዛኑ መጠበቅ አለበት፡፡ ለ30 ዓመታት የራሱን ማንነት የገነባን ሰው በአንዴ ቀይር የሚል መሆን አይገባውም፤›› ሲሉም ያሳስባሉ፡

  « Back to news archive